በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን፣ ፍትሕና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ከአገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የቀረበ የሰላም ጥሪ
እንደሚታወቀው ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ባወጣናቸው የአዲስ ዓመት የሰላም ጥሪዎች በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ለዘላቂ ሰላም መስፈንና እና የተረጋጋ የፖለቲካ አውድ ሽግግር ይጠቅማሉ ብለን ያሰብናቸውን የመፍትሔ አቅጣጫዎችና ምክረ ሐሳቦች ሰጥተናል። ከሰጠናቸው ምክረ ሐሳቦች ውስጥ ውሱንነቶች ቢኖሩባቸውም፣ ከሞላ ጎደል የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት መሻሻል፣ የሽግግር ፍትሕ ሒደት መጀመር፣ የሀገራዊ ምክክር የተሳታፊዎች ልየታ መጠናቀቅና የአጀንዳ ልየታ መጠናከር፣ እና የመሳሰሉት አዎንታዊ እርምጃዎች ሆነው አግኝተናቸዋል። ይሁንና አሁንም በቂ ትኩረት ያላገኙ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን ተረድተናል።
ለአብነትም በ2016 ብቻ በመላው ኢትዮጵያ ከ1,792 በላይ የግጭት ኩነቶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ በነዚህ ግጭቶችም በጥቅሉ ከ6,164 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። ይህም ማለት በግጭቶች ሳቢያ ብቻ በየወሩ በአማካይ 560 ሰዎች የተገደሉበት ዓመት ነበር (source: ACLED)። የነዚህ ግጭቶች ጦስም ከዘፈቀደ ግድያዎች ባሻገር፣ ለሰላማዊ ሰዎች አካል መጉደል፣ በሕፃናትና በሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃትን እንደበቀል እና ጥቃት መሣሪያ መጠቀም፣ ለዜጎች ከቀያቸው መፈናቀል፣ የሕክምናና የትምህርት ተቋማት መውደምና የሕፃናትና ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታ መቅረት፣ የመንቀሳቀስ ነፃነታቸውን ማጣት፣ አፈናና የአስገድዶ መሰወር መንሰራፋት፣ የዘፈቀደ እስሮች፣ በከተማዎች ውስጥ እና አቅራቢያ በሚደረጉ የተኩስ ልውውጦች ሳቢያ የሚፈጠር አለመረጋጋትና መሸበር፣ እንዲሁም እነዚህን ቀውሶች ያስከተሉት የኑሮ
ውድነት እና ጫና የዓመቱ አሳሳቢ ሁነቶች ነበሩ። እነዚህ ቀውሶች በተለይም በአማራ ክልል እንዲሁም በኦሮሚያ እና ሌሎች ክልሎችም ተባብሰው ተስተውለዋል።
በተጨማሪም ግጭቶች በተከሰቱባቸው የአማራ ክልልና በሌሎቹም የኢትዮጵያ ክፍሎች ለ10 ወራት ተፈፃሚ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ፣ የሲቪክ ምኅዳሩ በእጅጉ ሲጠብ፣ ጋዜጠኞችና የመብቶች ተሟጋቾች እንዲሁም የፖለቲካ አመራሮችና የምክር ቤት አባላት ጭምር ለእስር ተዳርገው በኢሰብዓዊ አያያዝ እንዲቆዩ መደረጋቸው ለዴሞከራሲ መጎልበትና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አሉታዊ እንድምታ እንደሚኖራቸው ይታወቃል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የምርመራ እና የሙግት ሥራቸውን እንዲያቆሙ የተለያዩ ጫናዎች የደረሱባቸው ሲሆን በይነመረብን (Internet) ማቆራረጥ በተለይም በአማራ ክልል፣ ለበርካታ ወራት ተፈፅሟል።
በመሆኑም መጪውን አዲስ ዓመት 2017ን ስንቀበል፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት፣ ነውጥ አዘል ግጭቶችን በሙሉ በማስቆም፣ እየከፋ የመጣውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፣ በተለይም በመጠንም በዓይነትም የተበራከቱ ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን እንዲሁም እየተንሰራፋ የመጣው ስርዓተ አልበኝነት ተከትለውን ወደ ቀጣዩ ዓመት እንዳይሸጋገሩ ፍትሕ እና ተጠያቂነትን በማስፈን እንዲሆን እኛ ከዚህ የሰላም ጥሪ ግርጌ ሥማችን የተዘረዘርን አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ይህንን ይፋዊ የአዲስ ዓመት የሰላም ጥሪ እና ምክረ ሐሳቦች እናቀርባለን።
1. ሰላም ይቅደም!
ሰላም ባልሰፈነበትና ባለፉት ዓመታት ያስተናገድናቸው ቀውሶችም ተገቢ እልባት ባላገኙበት ሁኔታ ወደ አዲሱ ዓመት የምናደርገው ሽግግር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ ስርዓት አልበኝነትን ለመዋጋትና ወንጀሎችን ለመቀነስ አስቸጋሪ እንደሚሆን እናምናለን።
በመሆኑም ዘላቂ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ ተብሎ ተስፋ የተሰነቀባቸው ሀገራዊ ምክክሩም ይሁን የሽግግር ፍትሕ ሒደቱ ያለ ዘላቂ ሰላም እውን እንደማይሆኑ በመረዳት፥ ሰላም የሁሉም ነገር ቅድሚያና መሠረት መሆኑን በመገንዘብ፣ መንግሥት እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከዓመታዊ አጀንዳዎቻቸው ሁሉ ለሰላም ቅድሚያ እና የሚገባውን ክብደት በመስጠት እንዲሰሩ አበክረን እንጠይቃለን።
ለሰላም ቅድሚያ ይሰጥ ስንል በአገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ጋር የተጀመሩ ንግግሮች እንዲቀጥሉ፣ ግጭቶችን የሚቀሰቅሱ አግላይ አሠራሮች እና ድንገተኛ ውሳኔዎች በአካታችነት፣ ግልጽነት፣ እና ምክክር እንዲተኩ፣ በሰላም ድርድሮች ወቅት ዜጎች ሒደቱንም ውጤቱንም እንዲያውቁ እንዲደረግ እንዲሁም የሰላም በሮች ሁሉ እንዲከፈቱ እና ሰላምና መረጋጋት ከሁሉም አጀንዳዎች ቅድሚያውን እንዲያገኝ ማለታችን ነው።
በዚህ መሠረት እኛ የዚህ የሰላም ጥሪ አቅራቢዎችም፣ እንደ ወሳኝ ባለድርሻ አካል፣ ኢትዮጵያ ለሰላም ቅድሚያ እንድትሰጥ የሚያግዙ ሥራዎችን በመሥራት ኃላፊነታችንን መወጣት እንደሚገባን በማመን፣
በአዲሱ 2017 ዓመት የሚመለከታቸውን አካላት በሙሉ ባሳተፈ መልኩ አገር ዐቀፍ የሰላም ጉባዔ እንዲካሄድ የሚጠበቅብንን ድርሻ ለመወጣት ቃል እንገባለን።
2. ግጭቶች በሰላማዊ መንገዶች ይፈቱ!
እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር፣ አሁንም ይሁን በታሪክ፣ የፖለቲካ ቅራኔዎቻችንንም ይሁን የመብቶች ጥያቄዎቻችንን በኃይል አማራጮች ለመፍታት የተጓዝንበት ረዥም ርቀት አገራችንን ማቆሚያ የሌለው የግጭት አዙሪት ውስጥ ከመክተቱም ባለፈ፣ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እና ኪሳራ ሲያደርስብን ቆይቷል። ግጭቶች በማናቸውም ሁኔታ ቢፈጠሩም እንኳ፣ እንደ አንድ ማኅበረሰብ ከነውጥ ይልቅ ሰላማዊ መንገዶችን በሙሉ አሟጦ በመጠቀም እና ትውፊታዊ የንግግር፣ የእርቅ እና የድርድር እሴቶቻችንን ቅድሚያ በመስጠት ዘላቂ መፍትሔና ሰላም ማፈላለግ ይጠበቅብናል።
ስለሆነም የትጥቅ ትግል ስልትን የመረጡ ወገኖች በሙሉ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰላም እና እፎይታ ሲባል ነውጥ ተኮር ከሆኑ ግጭቶች ታቅበው፣ በፍፁም ቅን ልቦና፣ ትዕግስት እና ቁርጠኝነት ለሰላም ውይይቶች እና ድርድሮች በራቸውን እንዲከፍቱ በድጋሚ እንጠይቃለን።
3. ፍትሕ እና ተጠያቂነት ይስፈን!
በኢትዮጵያ በሚካሔዱት የነውጥ አዘል ግጭቶች እና የሰላም እጦት ሳቢያ የስርዓት አልበኝነት መስፋፋት፣ የፍትሕ መጓደል፣ እንዲሁም ለተጠያቂነት የማያምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ። እንደማሳያም፣ የደቦ ፍርዶች መበራከት፣ አፈናዎች እና አስገድዶ መሰወሮች፣ የፆታ ጥቃትና በተለይ በቡድን መድፈር የዘወትር ክስተት መሆናቸው፣ ከአንድ የኢትዮጵያ ክፍል ወደሌላው በሰላም ወጥቶ መግባት አዳጋች መሆኑ፣ የሙስና መበራከት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት እና የዜጎች ብሶት አድማጭ ማጣት፣ ቀውሶቹን ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲባዙ እያደረጋቸው ነው። ይህ ሁኔታም ፍትሕን ለሚያጓድሉና ከተጠያቂነት ለማምለጥ ለሚምክሩ አካላት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
በመሆኑም በግጭቶች ዐውድ እና ከግጭቶች ውጪ የፆታዊ ጥቃት፣ ግድያ፣ እገታ እና አፈና የፈፀሙ፣ ፍትሕ ያጓደሉ፣ እየተተገበረ በሚገኘው የልማት ፖሊሲ ሰበብ በገጠርና በከተማ የሚኖሩ የዜጎች ሕይወት ላይ አደጋ የሚያስከትሉ እርምጃዎችን የወሰዱ፣ ዜጎችን ከቀያቸው ያፈናቀሉ፣ መንግሥታዊም ይሁኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች በሕግ የተጣለባቸውን የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶችና ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን ባግባቡ ባልተወጡ የፀጥታና የፍትሕ አካላት ላይ ተገቢው ክትትልና ምርመራ ተደርጎ ሕግን መሠረት ያደረገ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
4. ፆታዊ ጥቃቶች ትኩረት ይሰጣቸው!
ባሳለፍናቸው ሦስት የነውጥ አዘል ግጭቶች የተስፋፉባቸው ዓመታት፣ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች የበቀል መወጫ እና የጥቃት መሣሪያ ከመሆናቸውም ባሻገር፣ ለሴት ህፃናትና እና ለሴቶች የሚደረጉት
ጥበቃዎች እንዲዳከሙ አድርገዋል። በዚህም ሳቢያ ሕፃናት እና ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ አስገድዶ መድፈሮች፣ የህፃናት ጋብቻዎች፣ ግርዛት፣ እና ሌሎችም ልማዳዊ የሴት መብት ጥሰቶች በእጅጉ ተስፋፍተዋል። አልፎ ተርፎም ከግጭት ዐውድ ውጪ በሴት ህፃናትና በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጭካኔ የተሞላባቸው ፆታዊ ጥቃቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተዋል።
በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶች እና ፈፃሚዎች በሕግ የሚጣልባቸው ቅጣት አስተማሪ ያለመሆኑ ጥቃቶች እንዲደጋገሙ እና እንዲባባሱ አድርጓል የሚል ጠንካራ እምነት አለን። በተጨማሪም ተጎጂዎች ፍትሕን ፍለጋ ወደ ሕግ አካላት በሚቀርቡበት ጊዜ የሰውነት ክብራቸውን በጠበቀና ጉዳታቸውን ባገናዘበ መልኩ መስተናገድ የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸት የሚኖርበት ሲሆን፣ የሕክምናና መሰል ማስረጃዎችን የማቅረብ ጫና በተጎጂዎች ላይ የሚደረግበት ያልተገባና ሕጋዊ መሠረት የሌለው አሠራር በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል። አሁንም ግጭት እና የፖለቲካ ውጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ግለሰቦች ፆታዊ ጥቃትን እንደ የበቀልና ማጥቂያ መሣሪያ መጠቀማቸው እንደቀጠለ ነው። ይሁንና ለነዚህ ችግሮች ምላሽ የሚሰጡ ተቋማትና አካላት በግጭቶች ሳቢያ በተከሰቱ ቀውሶች የትኩረት አቅጣጫቸው ስለተበታተነና አቅማቸው ስለተዳከመ፣ ለችግሩ ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ እና ትኩረት መስጠት አልተቻለም።
በጥቅሉ በሴቶች ላይ በየቦታው በሚደርሰው በደልና ጥቃት ምክንያት ከዚህ ቀደም በሴቶች መብቶች ረገድ የተገኙ ድሎች እየተቀለበሱ ስለሚገኙ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት በጣምራ እንዲሁም በተናጠል ለዚህ አገራዊ አደጋ አስቸኳይ፣ ተመጣጣኝ እና አገር ዐቀፍ የሆነ ምላሽ እንዲሰጡ ጥሪ እናደርጋለን። በተለይም በአገሪቷ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ የተንሰራፋውን ፆታዊ ጥቃትን ለመቀነስ ቁልፍ ሚና ሊኖረው የሚገባውና በረቂቅ ደረጃ የቀረውን የፆታዊ ጥቃት መከላከያ ብሔራዊ ፖሊሲን እንዲፀድቅ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
5. የሲቪክ ምኅዳሩ ይጠበቅ!
በ2012 እና 2013 የተመዘገቡ የሲቪክ፣ ሚዲያ እና ዲጂታል ምኅዳሩን አስቻይ እንዲሆን አስተዋፅዖ ያደረጉ ሕጋዊ እና ተቋማዊ ለውጦች፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት እየተቀለበሱ መጥተዋል። እንደማሳያ የፖለቲከኞች እና የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች፣ ለዘፈቀደ እስር፣ ወከባ እና እንግልት መዳረግ፣ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት፣ መረጃ የማግኘት፣ የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ሕጋዊ መሠረት በሌላቸው ሰበብ አስባቦች እየተሸረሸሩ መምጣት እንዲሁም የሲቪክ ማኅበረሰብድርጅቶችእናአባላትላይ እየደረሰባቸውየሚገኘውወከባይጠቀሳል።ይህም፣ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሒደት እንቅፋት ከመሆኑም በላይ፣ ከላይ ለጠቀስናቸው ችግሮቻችን ሰላማዊ መፍትሔ የማፈላለግ ዕድል እንዲጠብ ምክንያት ሆኗል።
በመሆኑም የሲቪክ ምኅዳሩ መጠበቅ ለአገራችን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት፣ ፍትሕና ተጠያቂነት መስፈን፣ መሠረታዊ መብቶች መከበር እና ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ወሳኝ መሆኑን በመረዳት
መንግሥትለሲቪክማኅበራት፣ለመገናኛብዙኃንናጋዜጠኞች፣ ለማኅበረሰብአንቂዎችእንዲሁምለፖለቲካ ተዋናዮች በቂ ጥበቃ እንዲያደርግ እና መብታቸውንም እንዲያከብር እንጠይቃለን።
በመጨረሻም፣ እኛ የዚህ የሰላም ጥሪ አቅራቢ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዲሱ 2017፣ ለሰላም ቅድሚያ የሚሰጥበት፣ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ የሚቋጩበት፣ ፍትሕና ተጠያቂነት የሚረጋገጥበት፣ ሰብዓዊ መብቶች በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚከበሩበት፣ ፆታዊ ጥቃቶች አግባብ ያለዉ ቅጣት የሚያገኙበት፣ ተጋላጮች ከጥቃት የሚከለሉበት እንዲሆን እንመኛለን።
መልካም አዲስ ዓመት! —-
የዚህ የሰላም ጥሪ አቅራቢ ድርጅቶች
- የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች (Lawyers for Human Rights)
- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል (Ethiopian Human Rights Defenders Center)
- የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (Center for Advancement of Rights and Democracy)
- ሴታዊት(Setaweet)
- ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ ( Associations for Human Rights in Ethiopia)
- የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበረሰቦች ጥምረት (Network of Ethiopian Women Association)
- የኢትዮጵያየህግባለሙያሴቶችማህበር(EthiopianWomenLawyersAssociation(EWLA)
- የኢትዮጵያሴቶችመብቶችተቆርቋሪ(EthiopianWomenRightsAdvocate(EWRA)
- East African Initiative for Change (I4C)
10.የኢትዮጵያ ሠራትኞች መብቶች ተሟጋች (Ethiopian Labour Rights Watch)