ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሚኒስትሮች ም/ቤት ፀድቀው ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እየቀረቡ ያሉ አዳዲስ አዋጆች እና የአዋጅ ማሻሻያ ሃሳቦች በተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ላይ ጫና የሚያደረጉ፤ የአስፈፃሚዉን አካል ሥልጣን ከሚገባው በላይ የሚያጠናክሩ፤ በአንፃሩ ደግሞ የዳኝነት አካሉን ሚና ዝቅ የሚያደርጉ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግስት ለፌደራል መንግስት ተለይተዉ በተሰጡ ጉዳዮች ሕግ የማዉጣት ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡(ኢ.ፌ.ዲ.ሪ.ሕገ-መንግስት አንቀጽ 55)፡፡ ም/ቤቱ ይህንኑ ሓላፊነቱን ሲወጣ እንደማንኛዉም የመንግስት አካል፣ ምናልባትም በበለጠ ትኩረት እና ጥንቃቄ በሕገ-መንግስቱ የተደነገጉትን መርሆች በሙሉ በሚገባ መከተል ይጠበቅበታል፡፡ በመሆኑም ፓርላማዉ አዳዲስ ሕጎችን በሚያወጣበት ጊዜም ሆነ ያሉት እንዲሻሻሉ ረቂቅ ሲቀርብለት አዲስ የሚወጣዉም ይሁን የሚሻሻለዉ ሕግ በሃገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲሁም ዋስትና ያለዉ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን አበርክቶዉ ከፍ ያለ መሆኑን ማረጋገጥ ያለበት ከመሆኑም በላይ ሕገ-መንግስቱ የሃገሪቱ የበላይ ሕግ መሆኑን (ሕገ-መንግስት አንቀጽ 9)፤ ሰብዓዊ መብቶች ከሰዉ ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ፤ ማይጣሱ እና የማይገፈፉ መሆናቸዉን (ሕገ-መንግስት አንቀጽ10)፤ ይህን ምክር ቤት ጨምሮ በማንኛዉም ደረጃ የሚገኙ የፌደራል መንግስትና የክልል ሕገ አዉጪ፤ ሕግ አስፈፀሚ እና የዳኝነት አካሎች በሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ስር የተካተቱትን የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የማክበር እና የማስከበር ግዴታ እንዳለባቸዉ (ሕገ-መንግስት አንቀጽ13) እና የመንግስት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት (ሕገ-መንግስት አንቀጽ 12) ለአፍታም ሊዘነጋ አይገባም፡፡
ከዚህ አንፃር ባለፉት ጥቂት ወራት በሚኒስትሮች ምክር ቤት እየፀደቁ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እየቀረቡ ያሉ አዳዲስ ሕጎች እና ማሻሻያዎች በም/ቤቱ እየተስተናገዱ ያሉበት ሁኔታ ሕጎቹ ይዘዋቸዉ እየመጡ ካሉት አዳዲስ እና አነጋጋሪ ሃሳቦች አንፃር ለዉይይት በቂ ጊዜ በማይሰጥ ጥድፊያ እና ምናልባትም የምክር ቤቱ ዓመታዊ የሥራ ጊዜ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ብቻ የቀሩት መሆኑ ብቻ ታሳቢ ያደረጉ ከመሆናቸዉም በላይ በሕጎቹ ወይም በማሻሻያዎቹ ተካተዉ እየቀረቡ ያሉት አዳዲስ ሃሳቦችም በተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ላይ ጫና የሚያደርጉ፤የአስፈፃሚዉን አካል ሥልጣን በቀላሉ ባልተገባ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲዉል ሰፊ እድል በሚሰጥ ደረጃ የሚያጠናክሩ እና በአንፃሩ ደግሞ የሰብዓዊ መብቶች መከበር የመጨረሻዉ ዋስትና እንደሆነ የሚታመነዉን የዳኝነት አካሉን ሚና ዝቅ የሚያደርጉ መስለው ታይተዋል፡፡
እነዚህ ሕጎች ወይም ማሻሻያዎች በዋነኛነት የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 354/1995ን ለማሻሻል የቀረበዉን የማሻሻያ ረቂቅ እና የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጁን የሚመለከቱ ሲሆን ሌሎች ለም/ቤቱ እየቀረቡ ያሉ በዜጎች መብቶች ላይ ጫና ሊያደርጉ የሚችሉ አዋጆችም ከመጽደቃቸዉ በፊት በቂ ሕዝባዊ ዉይይት እንዲደረግባቸዉ ሰፊ ዕድል እንዲመቻች ድርጅታችን አጥብቆ ይጠይቃል፡፡